ቀጥታ፡

በክልሉ በግንባታ ላይ ያሉና ሌሎች የልማት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

ሚዛን አማን፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተገነቡ ያሉና ሌሎች የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አየለ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ከክልሉ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን በክልሉ በግንባታ ላይ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችንና ሌሎች የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል ።

የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የደንቢ ሎጅ፣ የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ እና ሌሎች የሌማት ትሩፋት ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አቶ ሰለሞን አየለ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ።

የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ተጠናቆ ሲመረቅ የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይበልጥ በማነቃቃት ለሃገራዊ እድገቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የክልሉን ጸጋዎች በማልማት ረገድ ከመንግስት ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶችና ምሁራን በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ምክክር በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል ።

የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ አዳዲስ የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚዎችን መርጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም