ቀጥታ፡

የአደይ አበባ ስታዲየምን በአንድ አመት ተኩል ማጠናቀቅ የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፦የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ጋር  የአደይ አበባ ስታዲየምን በአንድ አመት ተኩል ማጠናቀቅ የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የውል ስምምነቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ የኢትዮጵያ ማናጀር ሺን ቢን ተፈራርመዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በስፖርት ልማት ዘርፍ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

በነዚህ አመታት በአገር አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 500 ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ መካከለኛ እና አነስተኛ ስታዲየሞች ተገንብተዋል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 300 የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ነባር ስታዲየሞችን በማደስ እና በመጠገን ደረጃቸውን የማሻሻል ስራ በስፋት መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት የአደይ አበባ ስታዲየምን ከሰባት ወር በፊት  በ57 ሚሊዮን ዶላር ውል ተፈራርሞ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሒደቱ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

በዛሬው እለትም ከቻይናው ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ካምፓኒ ጋር በ 18 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ የውል ስምምነት መደረጉን አመላክተዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት በሚቀጥሉት 18 ወራት አንድ አመት ተኩል የቴክኖሎጂ ገጠማ፣ የጣሪያና የአጥር ስራ፣ የውስጥ እና የውጭ ማስዋብ እና ሌሎች መሰል ስራዎች የሚሰሩ ይሆናል ብለዋል፡፡

ቀሪ የግንባታ ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሚኒስቴሩ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

የቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ የኢትዮጵያ ማናጀርዪ ሲን ቢን በበኩላቸው፤ ግንባታውን በተቀመጠው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሙሉ ዝግጅት ያለ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡  

ስታዲየሙ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ አለም አቀፍ ስፖርታዊ ጨታዎችን ማካሔድ የሚያስችል ይሆናል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም