የአቪዬሽን ደኅንነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች ተላልፈዋል- ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የአቪዬሽን ደኅንነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች ተላልፈዋል- ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
አዲስ አበባ፤መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡-የአቪዬሽን ደኅንነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና በኢንዱስትሪው ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቀረበው ጥናት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
የሀገራችን የአቪዬሽን ደኅንነት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት መስፈርት መሰረት አስተማማኝና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ በርካታ ማረጋገጫዎች እየተሰጠ መሆኑን ገልጿል።
ዘርፉ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ ቢሆነም ከአቪዬሽን ደኅንነት ልዩ ባህሪና ውስብስብነት በመነሳት ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የጸጥታ ሁኔታው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተለይም በብሔራዊ አየር መንገዳችን ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ ቶላ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሲሳይ፤ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር እና በስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ ነቅተው በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የዘርፉን ስጋቶች፣ ክፍተቶች እና ተጋላጭነቶች በመገምገም እየተወሰዱ የሚገኙ የደኅንነት እርምጃዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ አሠራርንና ስታንዳርድን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ አገልግሎት መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በስፋት በተመከረበትና ውሳኔ በተላለፈበት መድረክ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ አባላት፤በቀጣይም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ አስጠብቆ ለመሄድ በየተቋማቱ የሚገኘውን አቅም አቀናጅቶ የመጠቀም ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የአቪዬሽን ደኅንነቱ የተረጋገጠና አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ውስጣዊና ውጫዊ ስጋቶችን፤ሀገራዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በተመንተን ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወቅታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
የሀገራችንና የአፍሪካዊያን ሁሉ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚደረገው የጋራ ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
በቀጣይ ዓለም ከደረሰበት ዕድገት አንጻር ኢንዱስትሪው የሚመራበት ሮድማፕ እንዲዘጋጅ እንዲሁም ወቅታዊ የኢንዱስትሪው ሁኔታ በየጊዜው እየተገመገመ እንዲመራ አቅጣጫ መቀመጡን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡