በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋትና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋትና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በማጠናከር አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማስፋት የጀመረቻቸው ስራዎች ፍሬያማ እየሆኑ መምጣታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዮሃንስ ፋንታ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ኤምባሲዎቿ በኩል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የመሳብና አዳዲስ የገበያ አማራጮችን የማስፋት ሥራን እየተገበረች ትገኛለች።
ሀገሪቱ በግብርና፣በአምራች ኢንዱስትሪ፣በማዕድን፣በኃይል መሰረተ ልማት፣በዲጅታል፣በቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ለኢንቨስትመንት ሰፊ አማራጮች እንዳሏት አመልክተዋል።
ሚኒስቴሩ በውጭ ግንኙነት ሥራዎቹ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራትን በዋና ተልዕኮነት እየተወጣ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
በተያዘው ዓመትም በኢትዮጵያና በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሞች የኢትዮጵያን ምርቶች ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መልካም ዕድሎችን መፍጠራቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም የምስራቅ አውሮፓ፣ የደቡብ አሜሪካ እና የእስያ ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የማግባባት ስራ መሰራቱንና ፍሬ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ከነባር የገበያና የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለግ ሥራን በመተግበር ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ በአፍሪካ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ምርቶች ተደራሽ ያልነበሩባቸው ሀገራት ላይ ገበያ በማፈላለግ ምርቶችን የመላክና ኢንቨስትመንት የመሳብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሰፊ የገበያ ዕድል ለመጠቀም ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም አምባሳደር ዮሃንስ አመልክተዋል።
አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን የማስፋትና የውጭ ኢንቨስተሮችን የመሳብ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተጀመሩ የቢዝነስ ለቢዝነስ ግንኙነቶች የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።