ቀጥታ፡

ዩኔስኮ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል-ዶክተር ሪታ ቢሶናውት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አለም አቀፍ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ገለፁ። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኢትዮጵያ በትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ላይ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል።

የተለያዩ ቅርሶችን በመመዝገብ ቅርሶቹን ጠብቆ የማቆየትና የመንከባከብ ስራ ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ያስመዘገበች አገር ናት። 

በዚህም እንደዩኔስኮ የኢትዮጵያ ተወካይ ኩራት ይሰማኛል ያሉት ዶክተር ሪታ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ተጨማሪ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገብ ቅርሶችን ለመንከባከብና ለመጠበቅ ከማስቻሉም ባለፈ ቅርሶቹን የሚጎበኙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግ የአካባቢው ማህበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል። 

ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሀብቶችን ለአለም ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ጠቅሰው በኢትዮጵያ ያሉ ዲፕሎማቶች በአገሪቱ ያሉ ቅርሶችን እንዲጎበኙ የማድረግ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። 

ዩኔስኮ መንግስት በቅርስ ጥበቃና በሌሎች ዘርፎችም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም