ለሀገራዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር የመሥራት ባህል ተጠናክሮ ይቀጥላል - የጋራ ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር የመሥራት ባህል ተጠናክሮ ይቀጥላል - የጋራ ምክር ቤቱ
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- ለሀገራዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር የመሥራት ባህል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ምክክር በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አየለ እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆንና ሀገራዊ ልማትን ለማሳለጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥነ-ምሕዳሩ አካታችነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳብ ልዩነት ውስጥ አንድ በሚያደርጉ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ላይ በትብብር የመስራት ባህል እየዳበረ መምጣቱንም አክለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ መሠረታዊ አጀንዳ ሰላም ነው ያሉት አቶ ሰሎሞን ችግሮች ሲፈጠሩ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፈቱበት አሠራርን በማስፈን ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ፖለቲካ ያለ ልማትና የሕዝብ አንድነት ትርጉም ስለማይኖረው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልሉ ያለውን እምቅ ጸጋ ወደ ሀብት መለወጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን ተቀራርቦ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
እስካሁን ባሉት ጊዜያት ግጭቶችን በጋራ በመፍታት ሰላምን ለማረጋገጥና ሕዝቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ የተሠራው መልካም ተሞክሮ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መስፍን መንገሻ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በዞኑ የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ለማረጋጋት አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
ዞኑ የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤዎች አክብሮ በጋራ ለመሥራትና እንቅስቃሴያቸውን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።
በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር መድረክ ላይ አዳዲስ ሥራ አስፈጻሚዎች እንደሚመረጡም ለማወቅ ተችሏል።