ቀጥታ፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ኃላፊ ሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ ከተመራ የምርመራ ቡድን ጋር በወንጀል ምርመራ ዙሪያ በኢትዮጵያ ፈደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በዱባይ ወንጀል ሠርተው በኢትዮጵያ የተሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገልጸዋል።

በቀጣይ በሁለቱም ሀገራት ተፈላጊ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በጋራ የወንጀል ምርመራ ቡድን በማቋቋም እና የልምድ ልውውጥ በማድረግ እንደሚሰራ መነጋገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ኃላፊ ሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ ለተደረገላቸው ትብብር ማመስገናቸውና በቀጣይ ለሚከናወኑ የጋራ የወንጀል ምርመራ ሥራዎች ወደ ዱባይ የሚያቀኑ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም