የሸዋል ኢድ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል - የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
የሸዋል ኢድ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል - የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ
ሐረር፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፦ የሸዋል ኢድ በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ አስታወቀ።
የሸዋል ኢድ በዓል ኢድ አል ፈጥር በተከበረ ከስድስተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ የሚከበር ክብረ በዓል ነው።
በዓሉም በየዓመቱ በክልሉ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚያጎለብት መልኩ በተለያዩ ሁነቶች በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር ስነ-ስርዓት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡም ይታወሳል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ክብረ በዓሉን አስመልክተው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮውን የሸዋል ኢድ በዓልን በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሲያከናውኑት የነበረው የዝግጅት ስራዎች ወደ መጠናቀቁ ደርሷል።
እንደ ቀድሞ ሁሉ ዘንድሮም በዓሉ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ በተለያዩ ሁነቶች በደመቀ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል።
በድምቀት የሚከበረው የዘንድሮው የሸዋል ኢድ በአል "የቅርስ ሐብቶቻችን ለቱሪዝም ልማታችን" በሚል መሪ ሀሳብ በድምቀት ይከበራል።
የዘንድሮው የሸዋል ኢድ በዓል አከባበርም ሰላምን፣ አብሮነትንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና አጎራባች ክልሎች በበዓሉ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
በክብረ በዓሉ ለጀጎል ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ አስተዋጽኦ ላበረኩቱ ባለድርሻ አካላት እውቅና እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
በዓሉ በሐረር የተከናወኑ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ስራዎች ጉብኝት የሚደረግበትና ገጽታ የሚገነባበት እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በበዓሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶች እንደሚታደሙና በከተማው የባህል ፌስቲቫልና ዐውደ ርዕይ እንደሚዘጋጅም አቶ ተወለዳ ጨምረው ገልጸዋል።