ለምርት ዘመኑ የበልግ አዝመራ ስራዎች ስኬት መረባረብ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ለምርት ዘመኑ የበልግ አዝመራ ስራዎች ስኬት መረባረብ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- ለ2017/18 ምርት ዘመን በበልግ አዝመራ የተያዙ እቅዶች እንዲሳኩ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስገነዘቡ።
በክልሉ በ2016/17 የመኸር እርሻ የተገኘውን አመርቂ ውጤት፤ በተያዘው የበልግ አዝመራ በመድገም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የተጀመረውን ሽግግር ማፅናት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በሁሉም የክልሉ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ተገቢውን ትኩረት ለበልግ አዝመራ ስራዎች በመስጠት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ እርጥበትን በአግባቡ ተጠቅሞ በምርት ዘመኑ ለበልግ አዝመራ ምርታማነት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አመራሩና ባለሙያው ከመቼውም ጊዜ በላይ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የማሻሻል፤ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማላመድ እንዲሁም የመስኖ ልማትና የኩታ ገጠም እርሻን የማስፋፋት ተግባራትን በተያዘው የምርት ዘመንም በማጠናከር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተጀመሩ የበልግ ስራዎችን ጨምሮ የሌማት ትሩፋት፤ የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት፤ የቡና እና ሌሎችም ኢንሼቲቮች አመራሩና ባለሙያው በጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፍ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ በመምራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲሰሩ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።