ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ ሃብት የመቋቋም አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን እና የአደጋ መከላከል አቅምን በሚመለከት ከግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) እንዲሁም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በተለይ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴንና የሜካናይዜሽን እርሻን የማስፋት እንዲሁም በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን ግብርና በመቀየር ዓመቱን ሙሉ ወደ ማረስ መገባቱን ጠቅሰዋል።
ይህም ምርትና ምርማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻገረ መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ልማት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) በበኩላቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት።
በዚህም ከለውጡ በፊት በመኸር 12ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ይታረስ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ወደ 20 ነጥብ 5 ሚለየን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበውን ምርት ከ293 ሚሊየን ኩንታል ወደ 608 ሚሊየን ኩንታል ምርት ከፍ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል በተጀመረው ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በመኸር ብቻ የሚገኘው ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ48 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
በ2011 ዓ.ም በ3ሺህ 500 ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ፥ አሁን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን በማንሳት ከዚህም 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተገኘ ያለው ስኬት የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመረውን ስራ እያገዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ናቸው።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል ፖሊሲ ተቀርፆ በሁሉም ክልሎች ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።