ለምርት ዘመኑ ወደ ሀገር ውስጥ የተጓጓዘው የማዳበሪያ መጠን ከ900 ሺህ ሜትሪክ ቶን ተሻግሯል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ለምርት ዘመኑ ወደ ሀገር ውስጥ የተጓጓዘው የማዳበሪያ መጠን ከ900 ሺህ ሜትሪክ ቶን ተሻግሯል - ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፦ ለ2017/18 የምርት ዘመን ግብዓት የሚውል እስከ አሁን ከ900 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታወቀ።
ለምርት ዘመኑ ግብዓት የሚውል 55 ሺህ ሜትሪክ ቶን ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ የጫነችው "MV ABBAY II" የተሰኘችው 19ኛዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ ደርሳ የማራገፍ ኦፕሬሽን መጀመሯንም ገልጿል።
መንግስት ለ2017/18 የምርት ዘመን ግብዓት የሚሆን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን(24 ሚሊዮን ኩንታል) የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል።
ከተያዘው እቅድ ውስጥ እስከ ትናንት ድረስ ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ጅቡቲ ወደብ መድረሱንና ከዚህም ውስጥ ከ900 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን ኢዜአ ከባለስልጣኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
118 ሺህ 956 ሜትሪክ ቶን ገደማ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
የተጓጓዙት የማዳበሪያ አይነቶች ዩሪያ እና ዳፕ ናቸው።
ማዳበሪያው በድንበር የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ እና በባቡር ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙንም ባለስልጣኑ ጨምሮ አስታውቋል።