ቀጥታ፡

ግድቡ በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የታቀደውን ኃይል ማሳካት የሚያስችል ውሃ ይዟል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- የቆቃ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግድብ በ2017 በጀት ዓመት ለማመንጨት የያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችል የውሃ መጠን መያዙን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡


 

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞርካ ኃይሌ እንደገለጹት ከአባ ሳሙኤል ቀጥሎ በ1952 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የቆቃ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላለፉት 65 ዓመታት አስተማማኝ ኃይል እያመረተ ይገኛል።

ማመንጫ ጣቢያው በ2017 በጀት ዓመት 134 ነጥብ 9 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት አቅዶ በ9 ወራት ውስጥ 119 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማምረቱንም ጠቁመዋል።

ከግድቡ የሚለቀቀው ውሃ በሕብረተሰቡ ላይ የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስ እንዲሁም ከማመንጫው በታችኛው ተፋሰስ ለሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ለመልቀቅ በግድቡ የሚገኘው ውሃ በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር እና በአዋሽ ተፋሰስ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግበት ተናግረዋል።

አሁን ላይ በግድቡ ያለው የውሃ መጠን ከባህር ጠለል በላይ 1586 ነጥብ 68 ሜትር ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከባህር ጠለል በላይ 1587 ነጥብ 01 ሜትር እንደነበር አስታውሰዋል።

በግድቡ ውስጥ የሚገኘው የውሃ መጠን ጣቢያው በቀሪ ወራት ያለምንም የውሃ እጥረት ኃይል እንዲያመነጭና ዓመታዊ ዕቅዱን እንዲያሳካ የሚያስችለው መሆኑንም አቶ ሞርካ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመላክትል።

ዕቅዱን ለማሳካት ከውሃ አስተዳደር ሥራው ጎን ለጎን ሣምንታዊና ወርሃዊ የጥገና ሥራዎች በዕቅድ ተይዘው እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።


 

ጣቢያው ከ65 ዓመታት በኋላም ሲገነባ ከተቀመጠለት 110 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ አማካይ ዓመታዊ የኃይል ምርት እያመረተ መሆኑን ገልፀው ለዚህም የኦፕሬሽንና የጥገና ክፍሉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ25 ዓመት በፊት በኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍሉ ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ መከናወኑንም አቶ ሞርካ ተናግረዋል።

አሁንም ጣቢያው ረጅም ዓመት ከማገልገሉ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ክፍሎች ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ እንደሚያስፈልገው ጨምረው ገልጸዋል።

የግድቡን ደህንነት ለመጠበቅና የእምቦጭ አረምን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በዕቅድ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የቆቃ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሦስት ተርባይን 43 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት የማምረት አቅም እንዳለውም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም