በክልሉ ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ ነው - የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ ነው - የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2017(ኢዜአ)፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ የሚገኙ ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡
ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች የአንድ ማህበረሰብ እሴትና መገለጫ ከመሆናቸው ባሻገር ለቱሪዝም መስህብነት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለገቢ ምንጭነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በክልሉ ሰላሳ ሁለት ብሔረሰቦች እንደሚገኙ ገልጸው ክልሉ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች የታደለ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦች ባህል፣ ታሪክና ቋንቋዎች ለምተውና ተጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ቢሮው የጥናትና የስነዳ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ2016 ዓ.ም የተጀመረውና በክልሉ የሚገኙ የሁሉም ብሔረሰቦች ቋንቋ ጥናትና ስነዳን በማጠናቀቅ ለብሄረሰቦቹ፣ ለህዝብ ቤተመጽሐፍት እና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡
የብሔረሰቦቹ አፋዊ ትውፊት የሆኑ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ተረቶችና እንቆቅልሾች በውስጣቸው በርካታ የማህበረሰቡን እሴት የያዙ ስለመሆናቸው ጠቅሰው፤ እነሱንም በተመሳሳይ የመሰብሰብና የመሰነድ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የብሔረሰቦቹን ቋንቋና ባህል ከማጥናት ባሻገር በካሪኩለማቸው አካተው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ለምተውና ተጠብቀው ለቱሪዝም ፍሰት፣ ለገቢ ምንጭነትና ለኢኮኖሚ ዕድገት እንዲውሉ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የህዝብ አንድነት፣ ሰላምና የጋራ ትርክት የሚያጠናክሩ እሴቶችን ጥቅም ላይ ማዋል አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የታቸኛው ኦሞ ሸለቆ የአርኪዮሎጂ ስፍራ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ የተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ናቸው፡፡
ክልሉ የበርካታ ባህልና ቅርሶች መገኛ እንደመሆኑ መጠን ተጨማሪ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ማስመዝገብ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የወላይታ ዘመን መለወጫ "ጊፋታ" ሁሉም ቅደመ ሁኔታ ተጠናቆ ወደ መጨረሻ ደረጃ መድረሱን፤ የጋሞ "ዱብሻ" ባህላዊ የዕርቅ ስርዓት እና የደራሼ "ፊላ" የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።