በረመዳን ወቅት የታየውን በጎነት፣ መተሳሰብና አብሮነት የእለት ተዕለት ኑሮ አካል ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በረመዳን ወቅት የታየውን በጎነት፣ መተሳሰብና አብሮነት የእለት ተዕለት ኑሮ አካል ማድረግ ይገባል
ጂንካ መጋቢት 21 /2017 (ኢዜአ):- በረመዳን ወቅት የታየውን በጎነት፣ መተሳሰብና አብሮነት የእለት ተዕለት ኑሮ አካል ማድረግ አንደሚገባ ተመለከተ ።
1 ሺህ 446ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በጂንካ የቀድሞው አየር ማረፊያ በኢድ ሶላትና ሌሎች ሀይማኖታዊ ክዋኔዎች ተከብሯል ።
በበዓሉ ላይ የአሪ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጀማል ሙሐመድ እንደገለጹት የረመዳን ወር መተሳሰብ ፣ፍቅርና አንድነት ጎልቶ የታየበትና ሀይማኖታዊ ትዕዛዛት የተተገበሩበት እንደሆነ አንስተዋል።
"የረመዳን ወር በጎነት፣ መተሳሰብና አብሮነት የታየበት ነው "ያሉት አቶ ጀማል፥ "በረመዳን ወር የተጠማን በማጠጣት፣ የታረዘን በማልበስ ፣ የተራበን በማብላት ያሳየነውን መልካም ተግባር የእለት ተዕለት ኑሯችን አካል ማድረግ አጠናክረን መቀጠል አለብን "ብለዋል።
የጂንካ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዑመርዲን ግርማ በበኩላቸው እንደገለፁት ፤ የኢድ አል ፈጥር በዓል ወንድማማችነት፣ አብሮነትና በጎነት ጎልቶ የሚታይበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል ።
"ሁላችንም ለሀገራችን ሰላምና ልማት እጅ ለእጅ መያያዝና አብሮ መስራት አለብን" ብለዋል።
"ህዝበ ሙስሊሙ ከወንድም ከእህቶቹ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር መኖር ይጠበቅብናል" ሲሉም አክለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ሰላምን ለማፅናትና ልማትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረጉን የገለፁት ደግሞ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ናቸው።
በቀጣይም ተግባሩን በማስቀጠል ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ተሳትፎውን እንዲያጎለብት ጠይቀዋል ።
የበዓሉ ታዳሚ አቶ ዱባለ ደምሴ በበኩላቸው "በረመዳን ወር ያለው ለሌለው በማካፈልና የተቸገሩትን በመርዳት በጎነትን በተግባር ያሳየንበት ወር ነው" ብለዋል።
በእስልምና አስተምህሮ ''ሰዎችን በበጎነት ታዛላችሁ፤ከክፉ ነገርም ትከለክላላችሁ!"የሚል አስተምህሮ እንዳለ ጠቅሰው፥ይህም የህይወታችን መርህ ሆኖ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው" ብለዋል።