በረመዳን ወቅት የታየውን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት ማስቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በረመዳን ወቅት የታየውን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት ማስቀጠል ይገባል
ሀዋሳ፤ መጋቢት 21/2017 (ኢዜአ):- ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ያሳየውን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት ማስቀጠልና ለሃገር ሰላም በአንድነት መቆም እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ሀጂ ሙስጠፋ ናስር ገለጹ፡፡
1446ኛው የኢድአልፈጥር በዓል በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ተከብሯል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚና የሰላምና የክልሎች ዘርፍ ሃላፊ ሀጂ ሙስጠፋ ናስር በወቅቱ እንደተናገሩት የረመዳን ወቅት የተለያዩ በጎ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡
"ሃይማኖታዊ አስተምሮው በረመዳን የጾም ቀናት ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረብን፣ ዘካ መስጠትንና የተቸገሩትን ስለመርዳት ያስተምራል" ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ያሳየውን የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት ማስቀጠልና ለሃገር ሰላም በአንድነት መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ አብዱልሽኩር አብዱልቃድር በበኩላቸው "የእስልምና አስተምሮ እርስ በርስ መተጋገዝን ያዛል" ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ አንድነትን በማጠናከርና በመተጋገዝ በክልሉ የተጀመሩ የልማት አጀንዳዎችን ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የረመዳን ወቅት በጎነት፣ሰላም፣ወንድማማችነትና አብሮነት የሚታይበት በመሆኑ መጠናከር እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አዳነ አገና ናቸው፡፡
ኢድ ሲከበር የተቸገሩና አቅመ ደካሞችን ማሰብ እንደሚገባ ገልጸው ህዝበ ሙስሊሙ በከተማው ለተጀመሩ ልማቶች ቀጣይነትና ለሰላም አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ አብዱልፈታ ሽኩሪ የረመዳን ጾም ከሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ የሚያሳልፉት በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢድ በዓልን ስናከበር ይህንን አብሮነት በማጠናከርና ኢትዮጵያ የብዝሃ ሃይማኖት ሃገር መሆኗን በማሳየት ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት የሚያከናውናቸው የመረዳዳት፣ መተጋገዝና አብሮነት እሴት በቀጣዮቹ ወራትም ማስቀጠል እንዳለበት የገለጸችው ደግሞ ወጣት ዘቢባ ጀማል ናት፡፡
በሃዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ በተከበረው 1446ኛው የኢድአልፈጥር በአል የኢድ ሶላትን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ተከናወነዋል፡፡