ከለውጡ ወዲህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ከለውጡ ወዲህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2017(ኢዜአ)፡- ከለውጡ ወዲህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ኢትዮጵያዊ የመጠያየቅና የመደጋገፍ እሴትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ተስፋ ብርሀን ቁጥር 2 የምገባ ማዕከል ለአቅመ ደካማ ወገኖች የዒድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ ያጋሩ ሲሆን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የኢትዮጵያውያን የመጠያየቅና የመደጋገፍ እሴትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሰው ተኮር ፕሮግራሞች የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከሎችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የምገባ ማዕከል ከመገንባት ጀምሮ የምገባ ስራውን እየደገፈ የሚገኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን አመስግነዋል፡፡
በምገባ ማዕከሉ በተከናወነው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ለማዕድ ማጋራቱ አመስግነዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ኡመር እና ወይዘሮ ዘይነባ ዳውድ መንግስት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ በኩል እያደረገው ለሚገኘው ሁሉ አመስግነዋል።
መንግስት አቅመ ደካሞችንና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖች ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደረገ ባለው ሰው ተኮር ተግባራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ኡመር ሙሃመድ ናቸው፡፡