ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካትና ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አቅም ፈጥሯል - አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 21/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋምና ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ መሆኑን የአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለጹ።

አስተባባሪው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ትልልቅ ዓላማዎች አሉት ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት ከዓላማዎቹ መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መርሐግብሩ ነባር ደኖችና የውሃ ሀብቶች የሚጠበቁበት እንዲሁም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ የሚያደርግ  እና ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

አረንጓዴ አሻራ በከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የማህበረሰብ ተሳትፎ እየተተገበረ የሚገኝ፣ ሁሉም ዜጋ ለአካባቢ ጥበቃ በአዲስ ዕይታ እንዲነሳ ያደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ መሆኗን ገልጸው፥ መርሐ ግብሩ ይህ ተጋላጭነት እንዲቀንስ እና የመቋቋም አቅም እንዲጨምር እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማሳካት ማስቻሉን አስረድተዋል።

መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ በመልካም እንዲነሳ ያደረገ ነው ያሉት አስተባባሪው፥ በርካታ ሀገራትም ከኢትዮጵያ ልምድ ለመቅሰም እየጠየቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ካርቦን ገበያ እየገባች ነው ያሉት አደፍርስ(ዶ/ር)፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርም በገበያው ውስጥ በቀዳሚነት እንድትጠቀም የሚያስችላት መሆኑንም ጠቁመዋል።

መርሐ ግብሩ የኢኮኖሚ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም