ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ በቀይ ባህር ጉዳይ ሁሉን አሳታፊ ትብብር እንዲፈጠር የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት- አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ በቀይ ባህር ጉዳይ ሁሉን አሳታፊ ትብብር እንዲፈጠር የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት- አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2017 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ በቀይ ባህር ጉዳይ ሁሉን አሳታፊ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲፈጠር የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ።
ኢትዮጵያ በብራዚል ብራዚሊያ በተካሄደው የብሪክስ የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ልዩ ልዑኮች ስብሰባ ላይ ተሳትፋለች።
በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ያሉ ግጭቶች እና ሰብዓዊ ጉዳታቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርን ባከበረ መልኩ ግጭቶች በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች እንዲፈቱ በየጊዜው የምታራምደው አቋም እንደሆነ አመልክተዋል።
ውይይት እና ዲፕሎማሲ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ቁልፍ መሆኑን ገልጸው የሰብዓዊ ቀውሶች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በየትኛውም መንገድ እና መገለጫ ለሽብርተኝነት ትዕግሥት የላትም ያሉት አምባሳደሩ የሽብርተኛ ቡድኖችን ለመዋጋት ዓለም አቀፍ ትብብር እና አጋርነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አምባሳደር ልዕልሰገድ በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ በሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ያልተቋረጠ ጥረት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ሱዳንን አስመልክቶ በአዲስ አበባ በትብብር ያዘጋጀቸውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ጉዳይ ኮንፍረንስ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት ለሱዳን ህዝብ የሚያደርጉትን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ የባህር ዳርቻ ዙሪያ ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት መካካል በርካታ የሕዝብ ቁጥር እንዳላት የገለጹት አምባሳደር ልዑልሰገድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ ላይ ሁሉን አሳታፊ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲፈጠር የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የብሪክስ የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ ስብስባ ባወጣው የጋራ መግለጫ በቀጣናው ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አሳስቧል።
በአዲስ አበባ ሱዳንን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመሆን ያዘጋጀችውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ጉባኤ መልካም ተግባር እንደሆነ መግለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።