ቀጥታ፡

በስንዴ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የተመዘገበውን ውጤት በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ለመድገም ትኩረት ተደርጓል-ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017 (ኢዜአ)፡-በስንዴ ልማት እና አረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የተመዘገበውን ውጤት በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ለመድገም ትኩረት ተደርጓል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ሆለታ ከተማ የብሔራዊ ሁለገብ የወተት ልማት ስልጠና ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

ሚኒሰትሩ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ሀገራዊ የወተት ምርት ፍላጎትን ማሟላት አልቻለችም፡፡

ይህ የሆነው የወተት ሐብት ልማቱን በእውቀት እና በክህሎት መመራት ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርናን የትኩረት ማዕከል ያላደረገ መንግስት አልነበረም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ሀብት ባለመመራቱ ውጤታማ አልሆነም ነው ያሉት፡፡

በዚህም ምክንያት የወተት ምርት ከውጪ ማስገባት ግድ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ካለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ወዲህ ግን የዘርፉን እምቅ አቅም በመለየት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት መደረጉንና አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በስንዴ ልማት ባከናወነቻቸው ስራዎች ከሀገር ፍጆታ ባሻገር ለውጪ ገበያ ማቅረብ መቻሏንና ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታገኝ ማስቻሉን ገልፀዋል፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልም በወሰደችው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም ተመሳሳይ ውጤት ማግኘቷን እና አድናቆት ማትረፏን አውስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በተለይ የእንስሳት ሃብት ልማት በእውቀት እና በክህሎት ለመምራት በርካታ የወተት ከብት አዳቃይ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በመላው ሀገሪቱ ወደ ሚገኙ ማዕከሎች ማሰማራት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ሀገራዊ የማዳቀል አቅም በዓመት ግማሽ ሚሊዮን ብቻ እንደነበር አውስተው፥በአሁኑ ወቅት ግን ዓመታዊ እቅዱ ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ማላቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ከብቶችን ማዳቀል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ በስንዴ ልማት እና አረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የተመዘገበውን ውጤት በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ለመድገም ትኩረት መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፥ የእንስሳት ሃብት ልማት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ብልጽግና የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

የማዕከሉ መገንባት ብቁ አዳቃይ ባለሙያዎችን በማፍራት የወተት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚረዳ መሆኑን ጠቅሰው፥በቀጣይ የሰለጠነ የሰው ሃብት የማፍራት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የወተት ልማትን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ ለምታከናውነው የልማት ስራ የዓለም ባንክ ትብብር ያደርጋል ያሉት ደግሞ የዓለም ባንክ ተወካይ ኢሊኦት ምግሄኒ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም