ቀጥታ፡

የፈዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራር አባላት የሠመራና ሚሌ ወደብና ተርሚናሎችን እንቅስቃሴ ተመለከቱ

ሠመራ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አመራር አባላት የሠመራና ሚሌ ወደብና ተርሚናሎችን እንቅስቃሴ ተመለከቱ

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ባህር ትራንሰፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)እንዳሉት፤የሠመራ ወደብና ተርሚናል ከጅቡቲ ወደብ አገልግሎት በ270 ኪሎ ሜትር ቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

የዛሬ 15 ዓመት ገደማ መቋቋሙን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤160 ሄክታር ሰፋት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሄክታሩ ለኮንቴይነር ተርሚናል አገልግሎት እንዲሰጥ የማልማት ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በአንድ ጊዜ 1ሺህ 180 ኮንቴይነር የማስተናገድ አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የሚሌ ወደብና ተርሚናል ደግሞ የተሽከርካሪ ጋራዥ ግንባታ መከናወኑን አሽከርካሪዎችን ከእንግልት የሚታደጋቸው ወሳኝ ግንባታ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ሲበላሹ ቶሎ ባለመድረስ ሲያጋጥም የቆየውን እንግልት የሚቀንሰ መሆኑን ገልፀው፥በዚህም ደህንነት በማስጠበቅ ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንዲሚቻል ነው ያስረዱት።

የመስመሮቹን የወደፊት ቀጣይነት ያለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን በመረዳት በወደብና ተርሚናሎቹ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም