ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ርዕሳነ መስተዳድሮች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2017 (ኢዜአ)፡- የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለ1446ኛው ዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት በአብሮነት እና በመደጋገፍ ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።
እስልምና ሰላም ነው የሰላም ምንጭ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዓሉን ስናከብር የኢትዮጵያን ሰላም በዘላቂነት መጠበቅ ታሳቢ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
አንድነትን በማጠናከር እና ድህነትን በማስወገድ ሀገርን ማልማት እና ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የደስታ እና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በዓሉን ስናከብር ለተቸገሩት በመራራት እና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በአንድነት እና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።
በበዓሉ የወንድማማችነት ትስስርንና አብሮነትን የሚያጠነክረውን ገዥ ትርክትን ማስረፅ ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሰላም፣የጤና፣የበረካና የደስታ እንዲሆን ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለመላው የእስልምና ተከታዮች መልካም የዒድ አል-ፈጥር በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል።
በተያያዘም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በመልዕክታቸው፥ ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳኑ ወር ሲያዘወትራቸዉ የነበሩ መልካም ተግባራትን በማስቀጠል፣ለአብሮነት እሴቶች መፅናት ፣ለዘላቂ ሠላም እውን መሆን፣ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለጋራ ልማት መፋጠን ከወትሮዉ በላቀ ትጋት እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተባበር መንፈስን ማደሻ እንዲሆን ተመኝተዋል።
በዓሉን ስናከብር ያለንን በማካፋል አቅመ ደካሞችን በመጠየቅና የተለመደውን እርስ በርስ የመረዳዳት ልምድ በማጎልበት መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በበዓል መልዕክታቸው ላይ እንዳሰፈሩት ህዝበ ሙስሊሙ ለዘመናት የገነባውን ፍፁም መልካም መስተጋብር የበለጠ በማጠናከር በሀገሪቱ ልማትና ሰላም ግንባታ ላይ ሚናውንም ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና እና የመተሳሰብ በዓል እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በታላቁ የረመዳን ወቅት ልዩነቶቻችን ሳይገድቡን የኢፍጣር ማዕድ በአብሮነት እንደተቋደስን ሁሉ፤ በዓሉን ኅብረትና አንድነታችንን ይበልጥ አጎልብተን ለጋራ ቤታችን ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና አብሮ በመቆም ማክበር ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስትም ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብሏል።
ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ክልሎች በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆንም ተመኝተዋል።