የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የአቅም ግንባታ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በአቅም ግንባታና ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ፣በድሮን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽንና በደኅንነት ቴክኖሎጂ ዘርፎች በጋራ የምርምርና ልማት ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል ተገልጿል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት ስምምነቱ ብሔራዊ ደኅንነትንና ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ሂደት ውስጥ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የውስጥ አቅምን ይበልጥ ያጎለብታል፡፡
በኢንዱስትሪውና በዩኒቨርሲቲው መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራልም ብለዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተደረሰው ስምምነት የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ የምርምር ውጤቶች የሆኑና ተቀባይነት ያላቸው የተሻሻሉ የድሮን ምርቶችን ለአፍሪካና ለዓለም ገበያ ጭምር ለማቅረብ የሚያስችል አቅምን በጋራ ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ተናግረዋል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያቸው በቴክኖሎጂ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራትና ቴክኖሎጂን በማልማት በማለማመድና በማሻሻል ረገድ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ከስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ውጤታማ ለማድረግ ዝግጁና ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ስምምነቱን መሠረት በማድረግም በድሮን ቴክኖሎጂ የተሻሉ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ አቅሞችን በፍጥነት በመገንባት ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ዶክተር ለሚ ተናግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ የሲቪል ፣ ወታደራዊና የደኅንነት አገልግሎት የሚሰጡ ድሮኖችን በማምረት ፈር ቀዳጅ ተቋም መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ የላከው መረጃ አስታውሷል።