ቀጥታ፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል

ሰቆጣ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፡-በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመመራት ባለሃብቱን በመደገፍና በማጠናከር የኢንቨስትመንት ዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ።

በሰቆጣ ከተማ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የ"ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" የማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ እንዳመለከቱት፤ ንቅናቄው በራስ አቅም የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ከጠባቂነት ለመላቀቅ እያስቻለ ነው።

በአካባቢው በግብርናና ማዕድን ዘርፎች ያሉ ጸጋዎችን በመለየት አልምቶ ለአገር እድገትና ለህዝብ ጥቅም ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመመራት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ እየተደረገ ያለው ጥረት ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው እንዳሉት፥ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 301 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት ተችሏል ብለዋል።

ፈቃድ ከተሰጣቸው ውስጥም 68 የሚሆኑት የፋብሪካ ግንባታ እያካሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመው፥ ስራ አቁመው የቆዩ 18 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ማምረት እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰዋልል።

በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንዱስትሪዎችን በመደገፍ ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ያስቻለ ነው።

በቀን 300 ኩንታል ሲመረት የቆየው ፋብሪካቸው በንቅናቄው በተደረገለት ድጋፍ የማምረት አቅሙን ወደ 500 ኩንታል ማሳደግ ማስቻሉን አስታውቀዋል።

በከተማው የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት የሆኑት አቶ ወንድሙ አብርሃ እንዳሉት፤ ንቅናቄው ባለሃብቱንና የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ፊት ለፊት በማገናኘት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስቻለ ነው።

በመድረኩ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ባለሃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም