ቀጥታ፡

የልማት አቅማችንን አሟጠን በመጠቀም እድገትን ማፈጠን ይጠበቅብናል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፤-በክልሉ ያለውን የልማት አቅም አሟጦ በመጠቀም የተጀመረውን እድገት ማፋጠን ይገባል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሰአዳ አብዱራህማን ገለጹ።

ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ መጋቢት 24ን ምክንያት በማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫና የብስክሊት ውድድር ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ጨፌ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሰኣዳ አብዱራህማን፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር)፤የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ጨፌ አፈጉባኤ ሳኣዳ አብዱራህማን፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ የማልማት አቅማችንን አሟጠን በመጠቀም የተጀመረውን እድገት ማፋጠን ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

በዚህም በተገኘው ድል የህዝቡ ጥያቄዎች እየተመለሱ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ በኩል የመጡ ስኬቶችን ለማስቀጠል የጋራ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በለውጡ ማግስት ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለመሻገር በተከናወነው ሪፎርም የተገኙ ስኬቶችን በመንከባከብ የነበሩትን ክፈተቶች ደግሞ ለመቅረፍ እንደሚሰራም አክለዋል።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)፤ እንዳሉት ከመጋቢት 24 ስኬቶች አንዱ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከለውጡ ወዲህ ሀገራችን በዘመናዊ የፖለቲካ ቅኝት የሀገር አንድነትን በማረጋገጥ ኢኮኖሚውን ማጠናከር መቻሉን ተናግረዋል።

ለግድቡ ስኬት የጠንካራ አመራሮች መሪነት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው የህዝቡ ሚናም የማይተካ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ፈተና በመቋቋም ለህዳሴ ግድቡ በላው አቅም እየተሳተፈ አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ እየተገባደደ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር) ናቸው።

የሀገር እድገት የሚመጣው በቅብብሎሽ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአሁኑ ትውልድ ህብረቱን አጠናክሮ ባለው አቅምና ችሎታ በልማት ላይ በመሳተፍ በኢኮኖሚ የዳበረችና አንድነቷን ያጸናች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ መትጋት አለበት ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ፤ህዝቡ ቦንድ በመግዛት በሌሎች መንገዶች ግንባታውን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከግለሰብ ህይወት ጋር የሚተሳሰር ወደ ከፍታ የሚወስድ ትልቅ በረከት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም