ቀጥታ፡

አገልግሎቱ ከዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ ተጨማሪ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል-አምባሳደር ፍጹም አረጋ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017 (ኢዜአ)፦ለህዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ ተጨማሪ ገንዘብ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።

ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ስድስት ሳምንታት ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰቡን መቻሉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥አገልግሎቱ በኤምባሲዎችና ቆንስላዎች አማካኝነት የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት፣በንግድና በቱሪዝም ዘርፍ በመሳተፍ ለሀገር ዕድገት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ዳያስፖራው በአገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ፣ህክምና፣ግብርና፣ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚሰማሩበት ኢንቨስትመንት መስኮች ናቸው ብለዋል።

ዳያስፖራው ለሀገር ገፅታ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ መሆኑንም አምባሳደር ፍጹም አረጋ ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ለዓለም በማስረዳት በኩል ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን ገልፀዋል።

ዳያስፖራው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢና በተለያየ መንገድ የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ 3 ሚሊዮን ዶላር ከዳያስፖራው ለመሰብሰብ የሚያስችል ዘመቻ በማዘጋጀት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት አርባ አምስት ቀናት ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡንም ገልፀዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግና ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ከአሜሪካ ሜሪላንድ የመጡት ነርስ ብሌን ሽመልስ የሀገሪቱን መልካም ገፅታ የሚገነቡ የልማት ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከጀርመን የመጡት ዶክተር አደራጀው ዋካ በበኩላቸው፥በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ባላቸው ሙያና ልምድ ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም