የታላቁ የህዳሴ ግድብ አፍሪካዊያን ታላላቅ የልማት ስኬቶችን በራሳቸው አቅም እውን ማድረግ እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ ነው-ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የህዳሴ ግድብ አፍሪካዊያን ታላላቅ የልማት ስኬቶችን በራሳቸው አቅም እውን ማድረግ እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ ነው-ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካዊያን ታላላቅ የልማት ስኬቶችን በራሳቸው አቅም እውን ማድረግ እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባ በፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ሀሳቦች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ምላሽና ማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማትና ዕድገት፣የሰላምና ደኅንነት፣ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን ዳሰዋል።
በኢኮኖሚ ልማት መስክ በሰጡት ማብራሪያም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣በአይሲቲና ማዕድን የብዝኅ ኢኮኖሚ መሰሶዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵዊያን የአንድነትና የሀገር ተስፋ ምልክት በሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማብራሪያቸውም ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተጠናቆ ለምርቃት እንደሚበቃ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፥ታላቁ የህዳሴ ግድብ ይህ ትውልድ በልማት ተጋድሎ ያስመዘገበው ዳግማዊ የዓድዋ ድል ነው።
ግዙፍ የኃይል ማመንጫ የልማት ፕሮጀክቱም ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር ኢትዮጵያ ኢ- ፍትሕዊ ልማትን መሸከም የማትችል ጠንካራ አገር መሆኗን ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ ሁለንተናዊ ድሎችን ማሳካት እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ ታሪካዊ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲፕሎማሲ ጫናዎችን በማለፍ በኢትዮጵያዊያን ትብብር ያለ አንዳች የውጭ ብድርም ሆነ እርዳታ ድጋፍ መሳካቱም በጋራ በመስራት ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያስመሰከረ ታልቅ የጋራ ብስራት መሆኑን አንስተዋል።
የዚህ ትውልድ አባል በመሆኑም ኩራትና ደስታ ይሰማኛል ብለዋል ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ።
ቅድመ አያቶች በጣሊያን ቅኝ ገዥ ወራሪ ኃይሎች ላይ ያስመዘገቡት የማይረሳ የድል ታሪክ የጥቁር ህዝቦች የዘመናት የይቻላል መገለጫ ሆኖ መዝለቁን አንስተዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብም አፍሪካዊያን በጋራ ሆነው ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም ማስመዝገብ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይልም የኢትዮጵያን ዕድገት በማስቀጠል ቀጣናዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።