ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የተመድ የንግድ እና ልማት ጉባዔ የጋራ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ጉባዔ (አንክታድ) በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ እና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ከተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ጉባዔ (አንክታድ) የስራ ኃላፊዎች ጋር በጄኔቫ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ፀጋአብ ውይይት ያደረጉት በድርጅቱ የፖሊሲ ትንተና እና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ጁኒየር ዳቪስ እና የአፍሪካ ዘርፍ በማደግ ላይ የሚገኙ እና የልዩ ፕሮግራሞች ኃላፊ ሃቢባ ቤን ባርክ ጋር ነው።

አንክታድ ለኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አምባሳደሩ፥ ኢትዮጵያ እ.አ.አ ማርች 2026 የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደቷን ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የአባልነት ሂደቱ እንዲሳካ የበይነ መንግስታት ተቋሙ የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ ቁልፍ የትብብር መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተነጋግረዋል።

በኢትዮጵያ እና አፍሪካ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም