ቀጥታ፡

ከሰሞኑ በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ በኢቤኤስ የተላለፈው ሀሰተኛ መረጃ ከ50 ዓመታት በላይ የቆየው የመጠፋፋትና የሴራ ፖለቲካ ውጤት ነው - ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦ከሰሞኑ በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ ኢቤኤስ የተላለፈው ሀሰተኛ መረጃ ከ50 ዓመታት በላይ የቆየው የመጠፋፋትና የሴራ ፖለቲካ ውጤት መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)ገለጹ።

ድርጊቱ ኢትዮጵያን የትርምስ እና የግጭት ማዕከል የማድረግ ዓላማ እንደነበረውም ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)፥ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ የተሰራውን የተቀነባበረ የሀሰት ፕሮግራም በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

የዚህ ዓይነት እኩይ ዓላማን ያነገቡ አካሄዶች ባለፉት ሰባት ዓመታት መልካቸውን እየቀያየሩ በታቀደ መልኩ ሲፈጸሙ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ላለፉት ከ50 ዓመታት በላይ የቀጠለው የፖለቲካ ልምምድ በርካታ ችግሮች ያሉበትና ኋላቀር መሆኑን ያነሱት ተጠሪ ሚኒስትሩ፥ በፍረጃ መጠፋፋት፣ የሴራ ትንተና፣ ሸፍጥ እና ውዥንብር መንዛት መገለጫዎቹ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

እንዲሁም የአክራሪነት እና ጽንፈኝነት ሰለባ መሆኑን እና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል የጠርዝ ፖለቲካ እንደሚራመድበት ገልጸዋል።

በዚህ ምክንያት ፖለቲካው ዴሞክራሲ እንዳይጎለብት አድርጓል ነው ያሉት።

ከሰሞኑ በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ ኢቤኤስ ቴሌቪዥን ያስተላለፈው የተቀነባበረ ሀሰተኛ ፕሮግራም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የተሻገረው የመጠፋፋትና የሴራ ፖለቲካ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ይህንን መጥፎና ሀገር ጎታች የፖለቲካ አካሄድ ለመቀየር መሰረታዊ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የተዛቡ ትርክቶች አሁንም ሀገርን እየበጠበጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ ከሰሞኑ በኢቢኤስ የተላለፈው ፕሮግራም የእነዚህ ነጠላ ትርክቶች ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጊቱ የኢትዮጵያን ትልቅነት የማይፈልጉ ጽንፈኞች ሀገሪቱን የጦርነት አዙሪት እና የትርምስ ማዕከል ለማድረግ የወጠኑት መሆኑንም አውስተዋል።

የሴቶችን ጥቃትና ሰብዓዊነትን ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል ሀሰተኛ ታሪክ በማዘጋጀት በህዝቡ ዘንድ ቁጣ እንዲቀሰቀስ አልመው የፈጸሙት ነው ብለዋል።

ከግጭት የሚያተርፉ በርካታ ጽንፈኞች ውዥንብር ለመፍጠር ቢሞክሩም አስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ የፅንፈኞችን ድርጊት በማውገዝ በቂ ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ አስተዋይነትም በዚህ ትርፍ ለማጋበስ ያሰቡ አካላት ሳይሳካላቸው መቅረቱን አመላክተዋል።

መገናኛ ብዙሃን በዘገባ ሥራዎቻቸው የሀገር እና የህዝብን ደህንነትና ጥቅም ማስቀደም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም