ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን አቅም የሚፈጥር ነው- የምጣኔ ሀብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን አቅም የሚፈጥር ነው- የምጣኔ ሀብት ምሁራን
አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በማጠናቀቅ ይመረቃል ሲሉ መግለጻቸው ይታወቃል።
ኢዜአም ግድቡ በቀጣይ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ምን ፋይዳን ያስገኛል ሲል የዘርፉን ሙህራን አነጋግሯል።
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ማክሮ ኢኮኖሚስት የሆኑት ተወልደ ግርማ (ዶ/ር)፥የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እንደ ሀገር ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይም የግድቡ ግንባታ ከጫፍ መድረስ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን በማሳደግ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬን እንድታገኝ ከማድረግ አኳያ ትልቅ አበርክቶ የሚኖረው ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ግድቡ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀገራዊ ሀብት በመጠቀም የሀገርን እድገት ብሎም ሉአላዊነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶችን መስራት እንደምትችል በተጨባጭ የምታረጋግጥበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
መንግስት በአሁኑ ጊዜ ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የሚሄድበት ርቀት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀም በኋላ መሰል ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ህብረተሰቡን በሳተፈ መልኩ መስራቱን መቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ሙህር ደረጄ ደጀኔ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዘለቄታዊነት ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ተግባራትን ማከናወን እና ለዘርፉ አስፈላጊ የሆነውን ኢነርጂ ተደራሽነት ማረጋገጥ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንድ ሀገር ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ከሚያነሷቸውና ከሚጠይቋቸው መሰረታዊ መስፍርቶች ውስጥ ዋነኛው በቂ የሆነ የሀይል አቅርቦት መኖሩን እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንንም ጥያቄ በተገቢው በመመለስ ኢትዮጵያ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን በኢንዱስቱትሪው ዘርፍ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማድረግ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት መጠናቀቅ በዘርፉ ላይ መነቃቃትን የሚፈጥር ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ግድቡ ለሀገሪቱ ከኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ ኢትዮጵያ የምግብ ሉአላዊነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝም ነው ሲሉ አክለዋል።
የግድቡ ግንባታ ወደሚጠናቀቅበት ምዕራፍ መድረስ የቻለው ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ልዩ ልዩ ድጋፎች መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ትብብር በሌሎች ልማቶች ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አክለዋል።