ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያከናውናቸው የቆየውን መልካም ተግባራት በሌሎች ወራትም ማጠናከር አለበት- ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያከናውናቸው የቆየውን መልካም ተግባራት በሌሎች ወራትም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ 1ሺህ 446ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፥ ለእምነቱ ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል ፈጥር በዓል አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የረመዳን ወር በአንድነት፣ በፍቅር፣ በአብሮነት፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍ ማለፉን ተናግረዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አልፈጥር በዓል ሲያከብር በጾም ወቅት ሲያደርግ እንደነበረው እርስ በርስ በመደጋገፍና ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሰላም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ እያንዳንዱ ዜጋ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

በተመሳሳይም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለመላው የእምነቱ ተከታዮች ለ1 ሺህ 446ኛውን ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላልፏል።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ፈትሁዲን ሐጂ ዘይኑ ሙቁና እና የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ሼህ ሁሴን በሽር ለበዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ሼህ ሁሴን በሽር በፆም ወቅት እስላማዊ እሴቶችን በማጎልበት ረገድ የታየው አብሮነት፣መተጋገዝ፣ መደጋገፍ እና ያለውን ማካፈል በዒድ ወቅትም መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዓሉን ማክበር ያለብን ስለሰላም፣ ስለፍቅር፣ በአንድነት ስለመቆም እና ስለወንድማማችነት በማሰብ እያጠናከርንም መሆን አለበት ብለዋል።

የአዲስ አበባ መጅልስ በዓሉ ኃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ከወጣቶች፣ከሴቶችና ከተለያዩ አደረጃጀቶች እንዲሁም ከመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።

የበዓሉ ተሳታፊዎች ከፀጥታ አካላትና ከአስተባባሪዎች የሚሰጡትን መመሪያዎች በማክበር በእስላማዊ ጨዋነት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም