ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ክብር የሚያስጠብቅና ሉአላዊነት የሚያስከብር አስተማማኝ ሰራዊት ተገንብቷል -ሌተናል ጄነራል በላይ ስዩም

ድሬዳዋ፤መጋቢት20/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ክብር የሚያስጠብቅና ሉአላዊነትን የሚያስከብር ዘመናዊና አስተማማኝ ፕሮፌሽናል ሰራዊት መገንባቱን የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል በላይ ስዩም ገለጹ።

የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የዘጠኛ ዙር ምልምል የሰራዊት አባላትን አሰልጥኖ አስመርቋል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል በላይ ስዩም፤ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ በመስጠት ተጨማሪ መልእክትም አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት በጀግንነቱና በጥብቅ ዲስፕሊን የሚታወቅ የሀገር መከታና በዓለም ላይ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል።

የሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከታ የሆነው ሰራዊቱ በላቀ ብቃት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ አቅም ታግዞ የሰው ሃይል ግንባታው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ክብር የሚያስጠበቅና ሉአላዊነትን የሚያስከብር ዘመናዊና አስተማማኝ ፕሮፌሽናል ሰራዊት ስለመገንባቱም አንስተዋል።

በመሆኑም የዛሬ ተመራቂዎች በሰለጠኑት የረቀቀ ወታደራዊ ስልት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በጀግንነትና በላቀ ብቃት ለማገልገል እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

የሀገርን ሰላም ለማደፍረስና የዜጎችን ደህንነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሊታገሱ እንደማይገባም አስገንዝበዋል።

የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ፤ተመራቂዎቹ በላቀ ወታደራዊ ሳይንስ በብቃት ሰልጥነው ያጠናቀቁና ለማንኛውም ሀገራዊ ግዳጅ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቆይታቸው የተግባርና ሳይንሳዊ እውቀቶችን በማቀናጀት በበቂ ሁኔታ መሰልጠናቸውን አረጋግጠው መከላከያን ይበልጥ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አቅም መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም