ቀጥታ፡

በመጋቢት 24 የተገኘው ለውጥ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ማሳደግ ያስቻለ ነው

መጋቢት፤20/2017 (ኢዜአ)፦በመጋቢት 24 የተገኘው ለውጥ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ ማሳደግ ያስቻለ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል መጋቢት 24 ቀንን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተደርጓል።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴው የተደረገው መጋቢት 24 የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣበት እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረት የተጣለበት ዕለትን ምክንያት በማድረግ ነው።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል ማያ፣ ጅማ፣ መቱ፣ ጊምቢ፣ ነቀምቴ፣ አምቦ እና በሌሎች የክልሉ ከተሞች እንደሆነ ታውቋል።

በማያ ከተማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባዔ ኤልያስ ኡመታ፣ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ፣ የማያ ከተማ ከንቲባ ኢፍራህ ወዚር (ዶ/ር) የዞኑና የከተማ አስተዳድሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚ
ያ ምክትል አፈ ጉባዔ ኤልያስ ኡመታ፤ በመጋቢት 24 የተገኘው ለውጥ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ማሳደግ ያስቻለ ነው ብለዋል።

በእነዚህ ዓመታት ችግሮችን በመቋቋም ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸው፤ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ህዝቡ ከመንግስት ጋር የጀመረውን ትብብር ማሳደግ እንዳለበት አመልክተዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነትም ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በጅማ ከተማ በተካሄደው ስፓርታዊ እንቅስቃሴ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፤ በክልሉ የግብርና ኢኒሼቲቮች እና በከተማ የተጀመረውን አስደናቂ የልማት ጉዞ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።

ለውጡ ይዞት የመጣውን የልማትና የህብረተሰብ ተጠቃሚነት እድሎች የበለጠ ማስፋትና ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርቡ ይቀጥላል ሲሉ ገለጸዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው፥ በአንድነት ተያይዘን ለልማት እና ለእድገት በመሮጥ ከድህነት ማምለጥ አለብን ብለዋል።

ባለፋት የለውጥ አመታት በከተማ ግብርና፣ በስራ እድል ፈጠራ ፣በኮሪደር ልማት እና በሌሎችም በርካታ የልማት ስራዎች ተተግብረዋል ነው ያሉት።

በነጌሌ ቦረና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ የተገኙት የምስራቅ ቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጁራ ኦዳ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውናችን መሰረት የአንድነታችንና የመተባበር ባህላዊ እሴቶቻችን መገለጫ በመሆኑ የሁላችንም የጋራ ሀብት ነው ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ እስኪሚበቃም የዞኑ ህዝብ የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የስፖርታዊ እንቅስቃሴው ተሳታፊ ጫላ ገደፋ፤ የአንድነታችንንና የማንነታችን መገለጫና ብሄራዊ ኩራት የሆነው የዚህ ታሪካዊ ግድብ መታሰቢያ ውድድር አሸናፊ በመሆኔ ኩራት ተሰምቶኛል ብሏል፡፡

ፋሲቱ ኮኮ በበኩሏ፤ ኢትዮጵያዊያን ከተባበርና አንድ ከሆንን ለሌሎችም የሚተርፍ ውጤት የማስመዝገብ አቅምና ብቃት አለን ብላለች፡፡

በመቱ ከተማ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎችም የጋራ የድል ምዕራፎቻችን በጋራ ተጠቃሚነታችን እና ሀገራዊ ብልጽግና የታጀቡ እንዲሆን ይበልጥ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል ወጣት ታምራት አሰፋ እና ወይዘሪት አያንቱ ተሾመ፤ መጋቢት 24 የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ትግል ውጤት፣ ሀገራዊ እድገት እና ብልጽግናችንን ማረጋገጥ የሚያስችላቸው ምዕራፍ የተከፈተበት ታሪካዊ ዕለት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም