በኢትዮጵያ ሶስተኛው የማሪታይም አካዳሚ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሊከፈት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሶስተኛው የማሪታይም አካዳሚ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሊከፈት ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማሪታይም አካዳሚ ለመክፈት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የማሪታይም ባለስልጣን ባሕረኞችን አሰልጥኖ ለዓለም ገበያ ለማቅረብና ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር እና በዩኒቨርሲቲው የማሪታይም አካዳሚ መክፈት የሚያስችለው ነው።
በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ሥር የሚከፈተው አካዳሚ ቀደም ሲል በሥራ ላይ ከነበሩት የባቦጋያ ሎጅስቲክስ እና ማሪታይም አካዳሚ እንዲሁም የኢትዮጵያ ማሪታይም ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት በመቀጠል ሶስተኛው እንደሚሆን ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም በሎጅስቲክስ አፈጻጸም ከአፍሪካ ቀዳሚ እንዲሁም ባህረተኞችን አሰልጥኖ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከመጀመሪያዎቹ አምስት የዓለም ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ራዕይ አንግቦ እንደሚገኝ በመረጃው አመልክቷል።