በአፍሪካ ለህጻናት መቀንጨር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አምራች ዜጋን ለመፍጠር መስራት ይገባል-አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ለህጻናት መቀንጨር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አምራች ዜጋን ለመፍጠር መስራት ይገባል-አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ለህጻናት መቀንጨር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት አምራች ዜጋን ለመፍጠር በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የአዳም ፋውንዴሽን መስራች እና የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ስነ ምግብ ለእድገት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በፈረንሳይ ፓሪስ ተካሄዷል።
በጉባዔው ላይ የአፍሪካ መሪዎች የስነ ምግብ መድረክ መስራች እና የአዳም ፋውንዴሽን የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ተሳትፈዋል።
አቶ ደመቀ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ እድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ለመቀንጨር እንዳይጋለጡ በማድረግ የዜጎችን እምቅ አቅም መጠቀም እና አምራች ዜጋን ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም የአዳም ፋውንዴሽን የስነ ምግብ ለእድገት ዓለም አቀፍ ጉባዔ (N4G) ግቦች እንዲሳኩ ስነ ምግብ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ለጋሾች የቅድሚያ ትኩረት እንዲያገኝ በቁርጠኝት እየሰራ ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ልዑካን እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የፋውንዴሽኑ ሊቀመንበር ከሌሴቶ ንጉስ እና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ የስነ ምግብ አጀንዳ ዋና አስተባባሪ ሌቲሴ ሶስተኛ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊና የስነ ምግብ ማሻሻያ ንቅናቄ አስተባባሪ አፍሻን ካን ጋር መክረዋል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን ሂደት የተመለከተ የጎንዮሽ ሁነት በጉባዔው ወቅት መካሄዱን በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተቋቋመው የአዳም ፋውንዴሽን በታህሳስ ወር 2017 ዓ.ም በይፋ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ነው።
ፋውንዴሽኑ በአፍሪካ መቀንጨርን መግታት ዋንኛ ግቡ አድርጎ እየሰራ ይገኛል።