ድርጅቱ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስመረቀ
ሰመራ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስመረቀ።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፤ የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሀላፊዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በተለያዩ አካባቢዎች በልማት ስራዎች በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
የሰመራ ወደብና ተርሚናል በሚገኝበት ስፍራ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ከ11 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ ሰመራ በሚገኘው ወደቡና ተርሚናል አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን በማገዝ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ደግሞ ድርጅቱ አጋርነቱን በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልፀዋል።