የአፈር ማዳበሪያን በአገር ውስጥ ማምረት ከምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው-የምጣኔ ሃብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር ማዳበሪያን በአገር ውስጥ ማምረት ከምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው-የምጣኔ ሃብት ምሁራን
አዲስ አበባ፤መጋቢት 20/2017(ኢዜአ)፡-የአፈር ማዳበሪያን በአገር ውስጥ ማምረት የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ከማሳለጥ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የሚያበረክት መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለፁ።
የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሃብት የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የግብርናውን ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ የግብዓት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በዘላቂነት መፍታት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች የሚያነሱት ነጥብ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የግብርናን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ይሁንና በተለይም የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ፍላጎት ጋር የተያያዘ ችግር መኖሩን ገልጸው፤ ለዚህም መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ብሎ ያቀደው ከውጭ የሚመጣውን ማዳበሪያ ለመተካት የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ደግሞ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊያን ሊያሳኩት የሚገባ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ወሳኝ የምርት ግብአት ከሚባሉት ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን፤ ከተገዛበት አገር ተጓጉዞ ለአርሶአደሩ እስኪደርስ ያለው ሰንሰለት ከፍተኛ ወጪና ጊዜ የሚፈጅ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ገልጸው፥ ለምጣኔ ሀብት ዕድገቱ የግብርናው ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም ነው ያነሱት።
ለግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር የግብዓት አቅርቦትና አዳዲስ ቴክኖሎጂ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ የአፈር ማዳበሪያ አንዱ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማስገባት ባለፈ በቦታ እርቀት ላይ ላሉ አርሶ አደሮች ድረስ በማጓጓዝ ለማቅረብ የእሴት ሰንሰለቱ ረጅም መሆኑን አንስተዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው እውን መሆን ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ምርቱን ለጎረቤት አገራት በማቅረብ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት ከምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ባለፈ ብሄራዊ ደህንነትን መጠበቅ መሆኑን የሚገልፁት ደግሞ በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ማክሮ ኢኮኖሚስት ተወልደ ግርማ(ዶ/ር) ናቸው።
ፋብሪካውን መገንባት የሀገርን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ አቅም ከፍ በማድረግ በኩልም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ይገልፃሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ከበደ ላቀው በበኩላቸው፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ኢትዮጵያ ስኬት እያስመዘገበችበት ላለው የግብርናው ዘርፍ የበለጠ መጎልበት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
በአትክልትና ፍራፍሬ የተጀመሩ ስራዎችንም ለማስፋት ማዳበሪያን በራስ አቅም ማምረት ለዘርፉ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተባበረ ክንድ ለፍፃሜ ማድረሱን ያነሱት ምሁራኑ፤የማዳበሪያ ፋብሪካውም ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክት እንደመሆኑ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።