ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የተቋማት ቅንጅት የበለጠ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የተቋማት ቅንጅት የበለጠ ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የተቋማትን ቅንጅት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስት ክላስተር ኮሚቴዎች የ2017 በጀት ዓመት የ8 ወራት እቅድ አፈፃፀምን ዛሬ ገምግመዋል።
በዚሁ ጊዜ ንቅናቄው እንደ ሀገር በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያጋጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመፍታት የማምረት አቅም እንዲጎለብት ማድረጉ ተገልጿል።
በተለይም ኢትዮጵያ ከውጭ በብዛት ታስገባቸው የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካቱ ስራ ውጤታማ መሆኑም ነው የተገለጸውው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ይሁንና ዘርፉ ከሚፈልገው ቅንጅታዊ አሰራርና መናበብ አኳያ የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑን አንስተው፣ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የአምስቱ ክላስተር ኮሚቴዎች ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን ለንቅናቄው ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ከግብዓት አቅርቦት፣ ከጥናትና ምርምር እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም ዘርፉ ለምጣኔ ሃብት ዕድገቱ ሚናውን የበለጠ እንዲያሳድግ ትብብሩን ማጎልበት ይገባል ነው ያሉት።
የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የፋይናንስ ድጋፍና በመሰረተ ልማት ላይ ያሉ ክፍተቶችን በተናበበ መልኩ መፍታት ያሻል ነው ያሉት።
ከንቅናቄው ክላስተር ኮሚቴ አባላት መካከል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪውን በማበረታታት ለተኪ ምርቶች ማደግ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችሉ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማቅረብ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ጸጋዬ ዘካርያስ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ያነሳሉ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዱ(ዶ/ር) በበኩላቸው እያንዳንዱ ተቋም ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረትን አድንቀው፣ ይህን የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስቱ የክላስተር ኮሚቴዎች የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ፣ የአቅም ግንባታና ምርምር፣ የኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ ናቸው።