አካዳሚው የአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል መሆን የሚያስችለውን አደረጃጀት መፍጠር አለበት - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
አካዳሚው የአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል መሆን የሚያስችለውን አደረጃጀት መፍጠር አለበት - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የአህጉሪቱ አመራር ልህቀት ማዕከል መሆን የሚያስችለውን አሰራርና አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን ጎብኝቷል።
በምልከታውም አካዳሚው ለሚያከናውናቸው የአመራር ልማት፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የአፍሪካ አመራር ልህቀት ማዕከል ለመሆን ለሚያደርገው እንቅስቃሴ አቅሙን በሰው ኃይል፣ በበጀትና በቴክኖሎጂ የተሟላ ማድረግ እንዳለበት ተመላክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ቤተልሄም ላቀው(ዶ/ር) አካዳሚውን የአፍሪካ ተቋም ለማድረግና በአህጉር ደረጃ ያለውን የአመራር ልማት ማሳደግ የሚያስችል ውስጣዊ መዋቅር ማደራጀትና ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
አካዳሚው በሀገር ውስጥ ካሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባውም ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴው የአካዳሚውን የማስፋፊያ ግንባታዎችም የተመለከተ ሲሆን ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አሳስቧል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ወይዘሮ መሰረት ደስታ አካዳሚው በሀገር ውስጥ ካሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር ያለው ትብብር እያጠናከረ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም እንዲረዳው በርካታ ስምምነቶችን መፈራረሙን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ወይዘሮ መሰረት ቋሚ ኮሚቴው የሰጣቸውን ግብረ መልሶች መሰረት በማድረግ የማስተካከያ ስራ እንደሚከናወን መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።