ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ለኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ለኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ ጥምር የጸጥታ ሃይሉ የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር በተዘጋጀ የፀጥታ እቅድ ላይ ውይይት አካሄዷል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በውይይቱ ላይ የፀጥታ አካላት በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት በዓሉ በስኬትና በደማቅ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ሕዝቡ ከዚህ ቀደም በተለመደ ሁኔታ ተከባብሮና ተዋዶ ያለምንም ስጋት፣ በነፃነት እና በደስታ በዓሉን ማክበር እንዲችል ከኃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች ከሕግ ውጭ የፀረ-ሰላምና ፅንፈኛ ኃይሎች መሣሪያ በመሆን ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ፣ በዜጎች ዘንድ መተማመን፣ አንድነትና አብሮነት እንዳይኖር እንዲሁም የመማር ማስተማር ሂደት በሰላም እንዳይቀጥል ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም ብለዋል፡፡
በዓሉ ሀይማኖትን ከሀይማኖት ጋር በማጋጨት ግጭት ለመቀስቀስ ከሚሞክሩት እንዳንድ ግለሰቦች በፀዳ ሁኔታ መከበር እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ግጭት ቀስቃሽ ፅሑፎች፣ ያልተፈቀዱ ምልክቶችና አልባሳት፣ የተለያዩ መፈክሮች እና ባነሮችን ይዞ በዓሉ ወደ ሚከበርባቸው ቦታዎች መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ስለመሆኑ መጠቆማቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ለጥምር የፀጥታ ኃይሉ አመራር እና አባላት ተገቢውን ኦረንቴሽን በመስጠት፣ በቂ የሰው ኃይል በመመደብ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።