ቀጥታ፡

ጽንፈኞች ካስተላለፉት ሀሰተኛ መረጃ ጀርባ ያለው ዋነኛ ዓላማ ትርምስና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መፍጠር ነው - የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ ጽንፈኛ ሃይሎች ብርቱካን ተመስገንን በሚመለከት ያስተላለፉት የሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ዋነኛ ዓላማ ትርምስና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መፍጠር መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ለኢዜአ እንዳሉት ሰሞነኛ የሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች አንድምታ በቀላሉ የሚታዩ ሳይሆን የፖለቲካ አለመረጋጋት መፍጠር፣ ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳትና ግጭት የመፍጠር እኩይ ዓላማ ያነገቡ ናቸው።

ኢቢኤስ በተሰኘው የሚዲያ ተቋም የተላለፈው የሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም አንድምታም ሀሳብ ያለቀባቸው ኃይሎች የህዝብ ለህዝብ ግጭት፣ ጥርጣሬና ባላንጣነት የመፍጠር እኩይ ዓላማ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ግጭት የገቡ አካላት መምህራንን ጨምሮ ንፁሃንን በጅምላ በመግደል ትውልድ አምካኝ፣ ሰላምና ልማትን የሚፃረር ተግባር ላይ መሰማራታቸውን ገልፀዋል።

አሁን ደግሞ የክልሉ ህዝብ የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ድርጊት እየተረዳ ሲመጣ ዘመቻ አንድነት በሚል ፕሮፓጋንዳ መክፈታቸውን ገልጸው፤ ለዚህም ህዝብን የሚያደናግር አጀንዳ እንደከፈቱ ነው ያነሱት።

ይህም መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ሀገራዊ ቀውስና ትርምስ የመፍጠር ግብ ያነገበ እንደሆነም ገልፀዋል።

የብርቱካንን ሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም በሚመለከት የተሰራጨው መረጃ ህዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ያለመ ቢሆንም በአስተዋይ ህዝብ መክሸፉን ነው ያነሱት።

ፅንፈኛ ኃይሎች ከማህበረሰቡ እሴት ውጭ የሆኑ በደሎች በህዝብ ላይ መፈፀማቸውን ገልፀው፣ የአንዲት ሴት ሀሰተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ በማራገብ የፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍጠር ስራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።

የብርቱካን ሃሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ስለዜጎች ክብርና ነፃነት በመቆርቆር ሳይሆን ግጭት ለመቀስቀስና የህዝብ አንድነት ለመሸርሸር ያለመ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ከማንም በላይ የተጋመዱና የማይነጣጠሉ ህዝቦች እንደሆኑ በመጥቀስ የህዝቦች አንድነት በየትኛውም ፅንፈኛ ቡድን እኩይ ሴራ የሚበጠስ እንዳልሆነ አንስተዋል።

በኢቢኤስ የተላለፈው ሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም የጥፋት ሀይሎች በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰሩና ለኢትዮጵያ ህዝብ እሴትና ክብር ያላቸውን ንቀት ያሳየ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሌም የህዝብ አንድነትን ለመሸርሸር እንደሚሰሩ ገልፀው፤ ህዝቡ እኩይ አጀንዳዎችን ወደ ጎን በመተው ከመንግሥት ጋር በመሆን ለሀገር ሰላምና ልማት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም