ፊቼ ጫምባላላ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ቅርስ ነው-አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች - ኢዜአ አማርኛ
ፊቼ ጫምባላላ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ቅርስ ነው-አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች

ሀዋሳ ፤መጋቢት 19/2017 (ኢዜአ) :- የሲዳማ የዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ለትውልድ የሚሻገር ቅርስ ነው ሲሉ በበአሉ የታደሙ የኦሮሞ አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች ገለጹ፡፡
የበዓሉ አከባበር የህዝቦች አንድነትና ፍቅር የታየበት መሆኑንም አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች ተናግረዋል።
የኦሮሞ ቱለማ አባገዳ ጎበና ኦላሬሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በፊቼ ጫምባላላ በዓል በተደጋጋሚ ተሳትፈዋል።
ፊቼ ጫምባላላን ጨምሮ የአደባባይ በዓላት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲደምቁ እድል የሚፈጥሩና አንድነትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአላቱን በጋራ ማክበር የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክርና ባህልን ለትውልድ እንዲሻገር የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ከበዓላት ባለፈ በልማት ጉዳዮችም መተባባርና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ የገለጹት አባገዳው የባህሉን እሴቶች ማሳደግና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሞ ገዳ ስርዓት ህብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው በበአሉ ከተለያዩ አካባቢዎች ልኡካን መታደማቸው የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
በአሉን በጋራ ማክበር ፍቅር፣ ሰላምንና አንድነትን በመፍጠር ለሃገር ግንባታ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ጠቁመው "እሴቱ ለትውልድ እንዲሻገር መስራት ያስፈልጋል " ብለዋል፡፡
"ፊቼ ጫምባላላ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል ነው" ያሉት ደግሞ ሀደ ሲንቄ ቱለማ አየሉ ይርቱ ናቸው፡፡
በበአሉ በመታደም ስለኦሮሞና ሲዳማ ህዝቦች አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር መስበካቸውን ተናግረዋል፡፡
ሀደ ሲንቄ ዘውዲቱ ጌታቸው በበኩላቸው "ከዋዜማው ጀምሮ የነበረው የፍቼ ጫምባላላ በዓል አከባበር የህዝቦችን አንድነትና ፍቅር ያየንበት ነው" ብለዋል፡፡
በአሉን በጋራ ማክበርም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
ዛሬ በሀዋሳ ሶሬሳ ጉዱማሌ በተከበረው የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል፡፡