ቀጥታ፡

ዲያስፖራው በሀገሪቱ የልማት ፕሮግራሞች ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፡- ዲያስፖራው በሀገሪቱ የልማት ፕሮግራሞች ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት  አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ፣ የጤና ሚኒስቴር እና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) በጋር በመሆን " የኢትዮጵያ ጤና ስርዓትን ለማሻሻል ከዲያስፖራው የሚጠበቀው ሚናና የዕውቀት ሽግግር " በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት አድርገዋል ።


 

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በዚህ ወቅት ፤ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ  ኢትዮጵያዊያን ባካበቱት ልምድ፣ ዕውቀትና አቅም  አገራቸውን እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡ 

አገልግሎቱ በውጭ ሀገራት በሚገኙ 53 የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች አማካኝነት ዲያስፖራውን የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው አባላቱ በሀገሪቱ በሚሰሩ የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች አሻራቸውን እያኖሩ ነው ብለዋል፡፡

ኮቪድ 19 በተከሰተ ወቅት በውጭ የሚኖሩ የህክምና ባለሙያዎች ሀገራችን በሽታውን የምትከላከልበትን የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን አንስተዋል ፡፡

የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው ፤የዲያስፖራ አባላት ከዚህ ቀደም በጤናው ዘርፍ በርካታ በጎ ተግባራትን ማከናወናቸውን ገልጸዋል ፡፡


 

በኢትዮጵያ የህጻናት ልብ ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ጥገና አገልግሎት እንዲሁም ለጤና ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል ፡፡

አባላቱ በሀገራችን ዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂ እንዲኖርና በውጭ ሀገር የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ሀገር ውስጥ እንዲጀመሩ የላቀ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ፕሮግራም ቀረጻና ትግበራ ማናጀር ወይዘሮ እማን ወንደሰን በበኩላቸው፤ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት እንዲያጋሩ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡


 

ይህም በኢትዮጵያና በጀርመን መካካል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል ፡፡

በአሜሪካ ሜሪላንድ የሚኖሩት ነርስ ብሌን ሽመልስ ፤ ባላቸው አቅም፣ ልምድና ክህሎት ሀገራቸውን ለማገልገል ምቹ ሁኔታ መኖሩን የተረዱበት መድረክ ነው ብለዋል ፡፡


 

በጀርመን የሚኖሩት ዶክተር አደራጀው ዋካ በበኩላቸው፤ ከሚኖሩበት አገር በመመላለስ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችን በሙያቸው እየደገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡


 

መድረኩ ድጋፋቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበትና ለቀጣይ ስራ ግብዓት ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም