በዞኑ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት ለሌሎች ዝናብ አጠር አካባቢዎች ትምህርት ሰጪ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት ለሌሎች ዝናብ አጠር አካባቢዎች ትምህርት ሰጪ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት ለሌሎች ዝናብ አጠር የኢትዮጵያ አካባቢዎችም ትምህርት ሰጪ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዝቋላ እና ደሃን ጨምሮ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተግባር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ተግባርን እንደሚሻ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የተከዜን ተፋሰስ በመስኖ የማልማት ስራም በየደረጃው የሚገኝ አመራር እና የአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብን እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
ተስፋ ሰጪ ጅምር ስራዎችን ማጠናከር፣ ማስፋት እና በቀጣይነት መፈፀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጅምር ተግባራት ለሌሎች ዝናብ አጠር የኢትዮጵያ አካባቢዎች ትምህርት ሰጪ መሆናቸውንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።