ቀጥታ፡

ተቋሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የህዝብን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና እምባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ገለጹ።

ዋና እምባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ እና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ከድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ጋር ተቀናጅቶ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ መክረዋል።

በውይይቱ ዋና እምባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በክልሎች በሚገኙ ስምንት ቅርንጫፎቹ በመታገዝ የህዝብን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል።

የመልካም አስተዳደር በደሎች ከመፈፀማቸው በፊት መከላከል ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ተቋሙ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች በምርመራ በማረጋገጥ የመፍትሄ ምክር ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው ተቋማት በማቅረብ በድርድር መፍትሄ እንዲሰጣቸው እያደረገ መሆኑን ነው ወይዘሮ ስመኝ የገለፁት።

በሚያከናውናቸው የክትትል፣ የምርመራና የማደራደር ስራዎች አበረታች ውጤቶች ቢገኙም አሁንም ከሚጠበቅበት ግብ አንፃር ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለበትም አመላክተዋል።

በቀጣይ ቅርንጫፎቹን በማጠናከር በየዘርፉ የሚስተዋሉ አስተዳደራዊ በደሎች ተፈትተውና በየመስኩ ጥሩ ግንኙነት ተፈጥሮ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ከዳር እንዲደርስ በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተለይም ሀገራዊው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በአግባቡ ተግባራዊ ሆኖ የህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ክትትሉና ድጋፉ እንደሚጠናከር በመግለፅ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ተቋሙ በመላው ሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እና የሚከሰቱ በደሎች መፍትሄ እንዲያገኙ እና ከበደል ነፃ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በድሬዳዋም ከመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ባሻገር የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚያደርገው ክትትልና ለሚከሰቱ ችግሮች የሚያቀርባቸው መፍትሄዎች ጠቃሚና ገንቢ መሆናቸውን በመጥቀስ።

አስተዳደሩ ከተቋሙ ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልፀው አስፈላጊው ትብብርና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም