ቀጥታ፡

ዚምባቡዌ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት - የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ ዚምባቡዌ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ የጸና ወዳጅነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ የአዲስ ዓመት መልዕክታቸውን ያስተላለፉበት ዓመታዊ ሁነት በሃራሬ ተካሂዷል።

በዚምባቡዌ የኢትዮጵያ አምባሳደር ራሽድ ሙሐመድ ከሁነቱ ጎን ለጎን ከዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ጋር ተወያይተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ እና ዚምባቡዌ ያላቸው ለረጅም ጊዜ ፀንቶ የቆየው የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ እንዲጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በሃራሬ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።


 

አምባሳደር ራሽድ ሙሐመድ የዚምባቡዌ መንግስት የሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በሌላ በኩል አምባሳደሩ በመጪው ሚያዚያ ወር በሀገሪቱ በሚደረገው የዚምባቡዌ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ላይ ከ10 በላይ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ እና የሀገራቸው ምርት እንደሚያስተዋውቁ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።

የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ እና ዚምባቡዌ መካከል እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያሳይ ኤምባሲው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም