ቀጥታ፡

በኢድ አል-ፈጥር በዓል የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ በኢድ አል-ፈጥር በዓል የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ ኃይል የመቆራረጥ ችግር እንዳያጋጥም ከተከሰተም በአፋጣኝ የአስቸኳይ ጥገና ሥራ ለመሥራት በየደረጃው ግብረ-ኃይል በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱን አመልክቷል።

ግብረ-ኃይሉም በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት በመካከለኛና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ ጭነት የማመጣጠንና ሌሎች የቅድመ-ጥገና ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብሏል፡፡


 

ህብረተሰቡም የኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት በተለይ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ባሉት ጊዜያት እንዲጠቀምም መልዕክት አስተላልፏል።

የቤት ውስጥ መገልገያ የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆን እንዳለባቸውም አገልግሎቱ ገልጿል።

ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም፣ በየአቅራቢያው በሚገኝ የተቋሙ ማዕከል በአካል በመቅረብ ወይም በ905 እና በ904 ነጻ የጥሪ ማዕከል በመደወል እንዲያሳውቅ አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም