ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ያላትን ዘርፈ ብዙ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ጽኑ ፍላጎት አላት- አምባሳደር ደሊል ከድር 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ያላትን ዘርፈ ብዙ ወዳጅነት እና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሊል ከድር ገለጹ። 

አምባሳደር ደሊል ከድር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አቅርበዋል።


 

አምባሳደር ደሊል በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እና በፓን-አፍሪካኒዝም መርህ ላይ የተመሰረተውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ የወዳጅነትና ወንድማማችነት ግንኙነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን አውስተዋል።  

ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በማድነቅ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሂደትን በማስተናገድ እና በማሰናዳት ላደረገችው ጉልህ አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈጻሚነት የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰው፣ ደቡብ አፍሪካ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ድጋፍ ማድረጓን እንድትቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

አምባሳደር ደሊል በሚኖራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን እና የደቡብ አፍሪካን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በባህል እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የትብብር ዘርፎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም