ታላቁ የህዳሴ ግድብ በፈጠረው የቱሪዝም እድል የክልሉን ተጨማሪ የቱሪስት መስህቦች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በፈጠረው የቱሪዝም እድል የክልሉን ተጨማሪ የቱሪስት መስህቦች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው
አሶሳ፤መጋቢት 18/2017(ኢዜአ):-የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጨመረውን የቱሪዝም ፍሰት ለሌሎች የክልሉ መስህቦች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
አገሪቷ ትኩረት ሰጥታ እየሰራችባቸው ካሉ የኢኮኖሚ አውታሮች አንዱ ቱሪዝም ነው።
በዚህም ያሉትን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦችን ከማልማት ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ ናቸው።
በትውልዱ ትጋት በመገባደድ ላይ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት ባለፈ ከዋነኞቹ የአገሪቷ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ነው።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ግድቡን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ሌሎች የክልሉን መስህቦች እንዲጎበኙ እና ቆይታቸውን ለማራዘም የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሚስኪያ አብደላ ለኢዜአ እንደገለፁት የህዳሴ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት በተጨማሪ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።
በዚህም ክልሉ የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም እና ሌሎች የክልሉን የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ ያለው የአስፓልት ግንባታና እና የኮሪደር ልማት ለዚህ ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና የእንግዳ ማረፊያ ቦታዎች በባለሀብቶች እየተገነቡ መሆኑንም አክለዋል።
የህዳሴ ግድቡን ለመጎብኘት ወደ አካባቢው የሚያቀኑ ጎብኚዎች በአቅራቢያው ያለውን የደጃዝማች ሙሐመድ ባንጃው ቤተመንግሥት እንዲጎበኙ ለማድረግ የእድሳት እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ከዚህም በተጨማሪ የሼህ ሆጆሌ ቤተ መንግሥት ፤ የችሎት አዳራሽና መካነ መቃብርም ክልሉ ካለው የቱሪስት መስህቦች ትልቁና አንዱ በመሆኑ ታድሶ ለጉብኝት ክፍት መደረጉን አንስተዋል።
በግድቡ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች በአስጎብኚነት የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ መጀመሩንም ሃላፊዋ ተናግረዋል።
ጎብኚዎች በሁለት አቅጣጫ ወደ ክልሉ ይገባሉ ያሉት ሚስኪያ፤ በዚህም አሶሳ እና ግልገል በለስ ከተማን የማስዋብ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ግድቡ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ አይነተኛ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።
በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ እና ተጨማሪ የገቢ አቅም እንዲፈጠር ግድቡ የሚፈጥረው የቱሪዝም እድልን ለመጠቀም እየተሰራ ነው።
በዚህ ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ከ49 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በክልሉ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን መጎብኘታቸውን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።