ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የላቀ ውጤታማነት ተቋማት የተቀናጀ አሰራርን እንዲተገብሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19/2017 (ኢዜአ)፦ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የላቀ ውጤታማነት ተቋማት የተቀናጀና የተናበበ አሰራርን መተግበር እንዳለባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስት ክላስተሮች የ2017 በጀት ዓመት የ8 ወራት እቅድ አፈፃፀም እየገመገሙ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፥ በግምገማው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፥ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለውጥ ማምጣት የቻሉ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የአምስቱ ክላስተር ኮሚቴዎች ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን ለንቅናቄው ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ጠቅሰዋል።

የአምራች ዘርፉ ዕድገት የሁሉንም ተቋማት ድጋፍና ርብርብ እንደሚጠይቅ አንስተው፣ ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የበለጠ ውጤታማነት የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማፋጠን የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው ይህን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥና የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ያሉ ክፍተቶችንም በተናበበ መልኩ መፍታት ያሻል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪውን በማበረታታት ለተኪ ምርቶች ማደግ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስቱ የክላስተር ኮሚቴዎች የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ፣የአቅም ግንባታና ምርምር፣ የኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም