የመጀመሪያው የኢትዮ-ዩናይትድ ኪንግደም የፖለቲካ ውይይት በለንደን ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የኢትዮ-ዩናይትድ ኪንግደም የፖለቲካ ውይይት በለንደን ተካሄደ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም የፖለቲካ ምክክር ስብሰባ በለንደን ከተማ ተካሂዷል።
የፖለቲካ ምክክሩ የሁለቱ ሀገሮች የጋራ ቅድሚያ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መካሄዱን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በተለይም በኢኮኖሚና የጋራ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ እስከ አሁን የነበሩ ትብብሮችን አፈጻጸም በመገምገም ወደፊት አጋርነቱን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ውይይት ተደርጓል።
በዚህ መሰረት በኢኮኖሚ ዘርፍ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ሰፊ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣አዳዲስ ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች መከፈት፣ ለኢንቨስተሮች የተፈጠረውን ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታና ሰፊ እድል መፍጠሩ ተመላክቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለሃብቶች እድሉን ተጠቅመው በኢትዮጵያ መግባት እንዲችሉ ለማበረታታት፣ የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን በጋራ ለመፍታትና የአገራቱን ህዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ትብብሩን ለማሳደግ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በሰላምና ፅጥታም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ትብብር ጠንካራ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
በቀጣይም ትብብሩን በማጠናከር ስምምነት ላይ መደረሱን ኤምባሲው በመረጃው አመልክቷል።